ሰሞኑን ኢህአዴግ ጉባኤውን ሲጨርስ “አድርባይነት አሰጋኝ” ብሎናል። አባላቶቼ አድርባይ ሆነዋልና በዚህ ከቀጠልኩ እሰምጣለሁ የሚል ስጋት እንዳለበትም አስታውቆናል። ከፍርሃቻው ብዛት የተነሳ አድርባይነትን ለመዋጋትና “መድረክ ላይ ለመጥለፍ” በቁርጠኛነት እንታገላለን ብለው አቋማቸውን ነግረውናል። የሚገርመው ግን አድርባይነትን የፈጠረና ያነገሰው ራሱ ኢህአዴግ መሆኑን መዘንጋቱ ነው።
ኢህአዴግ አድርባይ ሚዲያዎች አሉት። አድርባይ ባለሃብቶች አሉት። ኢህአዴግ አድርባይ የኔቢጤዎች አሉት። ኢህአዴግ አድርባይና የማደናገሪያ ፕሮጀክቶች አሉት። ኢህአዴግ አድርባይ ድርጅቶች እንጂ ነጻ ድርጅቶች የሉትም። ኢህአዴግ አድርባይ ባለስልጣናት እንጂ ነጻ አመራሮች የሉትም። ሁሉም አድርባዮች ተጠሪነታቸው ለህወሃት ስለሆነ ተጠያቂውም ራሱ የኢህአዴግ ሾፌር ህወሃት እንጂ ሌሎች ሊሆኑ አይገባም። “ፈጣሪያቸው” የሚገመግማቸው፣ እነሱም አምነው የሚገመገሙት ታማኝ አድርባይ ስለሆኑ ብቻ ነው።
አሁን እየተለመደ የመጣው የመፈክርና የቀረርቶ ጉዳይ አጥወልውሎ የሚጥል ደረጃ ያደረሰንም ለዚህ ነው። ቃላት ማምረትና ማራባት የተካነበት ኢህአዴግ በየጊዜው የሚፈለፍላቸው ቃላቶች እያንገፈገፉን ነው። በተለይም ታላላቅ ዋጋ ባላቸው “ውድ” ቃላቶች ላይ አደጋ እየፈጠረም እንደሆነ ይሰማናል፤ ይጫወትባቸዋል። አድርባይ ሚዲያዎችና አድርባይ ጋዜጠኞች የማከፋፈሉን ስራ ይሰራሉ። ይህ በአገር ደረጃ የተንሰራፋው አድርባይነት ለኢህአዴግ ስጋቱ አይደለም፤ ኩራቱ እንጂ!!
ይህንን ያነሳነው ወድደን አይደለም። ባለፈው ሳምንት ባወጣነው የአባይ ግድብ ከግማሽ በላይ የኢትዮጵያ አይደለም የሚል ዜና አድርባይ እንድንሆን ያሳሰቡን በመኖራቸው ነው። ስለ አባይ ግድብ ያሰራጨነው ዜና ያስደነገጣቸው በርካቶች ናቸው። የአባይ ግድብ መገደብ እውን መሆን አለበት። አባይ ተገድቦ አገር መልማት አለበት። አባይን ለልማት ለመጠቀም ለሚገጥም ችግር ሁሉ ሁላችንም “ልዩነት” ሳይገድበን ዘብ እንቆማለን!! ግን የግልጽነት ጥያቄ ያሳስበናል። ያስጨንቀናል። “በልማትና ዕድገት” ስም የተድበሰበሱ ውሎችና ስምምነቶች እኛንም ሆነ መጪውን ትውልድ ዋጋ እንዳያስከፍሉን ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ እናምናለን። በዚህ ጉዳይ ላይ አድርባይነት የለም!!