Thursday, October 10, 2013

ድሆችን ያፈናቀለው “ኢንቨስትመንት” ዕዳ ዋጠው

anuak man“መሬታችንን ለምን እንነጠቃለን?” በማለት የጠየቁ ተገድለዋል። ተገርፈዋል። ታስረዋል። አሁን ድረስ እስር ላይ የሚገኙ አሉ። ባዕድ እንኳን ባልሞከረው የከፋ ጭካኔ በከባድ መሳሪያ በተደገፈ የጦር ሃይል የተወለዱበትን መሬት እንዲለቁ የተገደዱ አዛውንቶች ላይ የተፈጸመው ግፍ እስከ ወዲያኛው የሚያሽር አይደለም። በሌሊት እርቃናቸውን ከሚያርፉበት ታዛ ስር ነፍጠኛ ሰራዊት እንዲከባቸው እየተደረገ የተፈጸመው አስነዋሪ ግፍ ጊዜ የሚጠብቅ እንደሆነ በየጊዜው የሚገለጽ ነው።
“የዘራሁትን ሳላነሳ በዶዘር ማሳዬን ጠረጉት፣ በዶዘር እርሻዬ ውስጥ ገብተው አረሱት፣ መሬቴን ለምን ትወስዳላችሁ? የት ልትወስዱኝ ነው? ያሸተውን በቆሎዬን መነጠሩት። ምን ላደርግ እችላለሁ። መሳሪያ የያዙ ወታደሮች ከበውኛል፣ ጠዋት ስነሳ ማሳዬ ባዶ ሆኖ አገኘሁት … ” ይህ ሁሉ የበደል ሰቆቃ ነው። በምስል ተደግፎ የቀረበ ህሊናን የሚሰብር መረጃዎች አሉ።
አንድ የአካባቢው ነዋሪ “ሰላማዊ ህዝብ፣ በቅጡ የሚለብሰው እንኳን የሌለውን ህዝብ፣ አሮጊቶችን፣ አዛውንቶችንና ህጻናትን
ሲገድሉና ሲያሰቃዩ የቆዩት ለዚህ ነው? ለዚህ ኢንቨስትመንት ነው
ያ ሁሉ የተፈጥሮ ደን ወድሞ ከሰል እንዲሁን የተደረገው?

                                                                                                                      Photo: IC magazine      
 ገንዘብ ሳይሆን የከሰል ጆንያ ይዘው ክልሉን እንዲቀራመቱ የሚፈቅዱት ክፍሎች ስለጊዜና ስለዘመን ለምን አያስቡም?” ሲል ይጠይቃል። በማያያዝም “70 ከመቶ የሚሆኑት ባለሃብቶች የትግራይ ሰዎች መሆናቸውን እናውቃለን። መረጃውም አለን። እባካችሁ የተጨቆናችሁ የትግራይ ወንድምና እህቶች እባካችሁን በስማችሁ እየተፈጸመብን ያለውን በደል ተቃወሙ” ሲል ለጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ አስረድቷል።
አዛውንቱ ጸሐይ ለመሞቅ ታዛ ስር ቁጭ ባሉበት (በፎቶው የሚታዩት አይደሉም) ከሙሉ ቤተሰባቸው ጋር የጥይት ራት የተደረጉበት ኢንቨስትመንት አስቀድሞ የተገለጸ ቢሆንም መጨረሻው ሌብነት እንደሆነ ኢህአዴግና ራሱ ድርጅቱ ማመናቸው ተሰማ። አቶ መለስ ሲጀነኑበት የነበረው ኢንቨስትመንት አውላላ ሜዳ ላይ የተደፋ ስለመሆኑ የተጠየቁት አቶ ኦባንግ ሜቶ “እኛን የሚያሳስበን በሊዝ ያልተሸጠው መሬት ነው” በማለት አቶ መለስ የተናገሩትን በማስታወስ “ህዝብን የማይሰማ ድርጅት ዞሮ ዞሮ ከውርደት አይድንም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። የሰሙት ዜና የሚጠበቅ እንደሆነ ያመለከቱት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ “ሚዲያዎች በነካ እጃቸው ስለ ሰለባዎቹም ይተንፍሱ” ሲሉ ጠይቀዋል።
ኦገስት 31/ 2013 የታተመው የጎልጉል ዜና “የኢትዮጵያን ለም መሬት ከተቀራመቱት ኢንቨስተሮች መካካል አንዱ የሆነው የህንዱ ካሩቱሪ ከኢትዮጵያ ለቅቆ የሚወጣበት ጊዜ መቃረቡን ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ክፍሎች ለጎልጉል አስታወቁ። አበዳሪዎችና ባለ አክሲዮኖች ፊታቸውን እንዳዞሩበትም ታውቋል። ከዚህ በተጨማሪም በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ባዶ ዋይታ የሚያሰማው ኢህአዴግ የያዘው አዲስ አቋም ድርጅቱንና ከድርጅቱ ጋር የቀረበ ግንኙነት አላቸው የሚባሉትን ሃሳብ ላይ ጥሏል” ሲል መዘገቡ ይታወሳል።
በዚሁ ዘገባ ላይ በቦታው ኢህአዴግና ጭፍሮቹ መካከል ሆነው የተካሄደባቸውን የመሬት ነጠቃ በመቃወምና ለሚመለከታቸው አካላት በማሳወቅ ጀብድ ለሰሩት “… በቦታው ላይ ሆናችሁ ለህይወታችሁ ሳትፈሩ ይህንን መረጃ የሰጣችሁ ሁሉ የአገር ጀግኖች ናችሁ፤ አሁን አትታወቁም። አሁን ልንገልጻችሁ አንችልም። ጊዜና ወቅት ጀግንነታችሁን እስኪገልጹት ግን አትረሱም። ልትረሱም አትችሉም። ብዙ ባይነገርላችሁና ባይዘመርላችሁም ታላቅ ስራ ሰርታችኋልና ክብር ይሁንላችሁ” ሲሉ አቶ አባንግ ያስተላለፉት መልክትም ከዜናው ጋር ተካትቶ ነበር።
“በእውቀት ላይ የተመረኮዘ፣ በእቅድ የተያዘ ትግል እያካሄድን እንደሆነ በገለጽኩበት ወቅት ካሩቱሪ በኪሳራ ከኢትዮጵያ ምድር እንደሚወጣ ተናግሬ ነበር። አሁን ጉዳዩ ያለው የኢትዮጵያን ድንግል መሬት በሳንቲም የቸበቸቡትና ያስቸበቸቡት የጥቅም ተጋሪዎችና ደላሎችን ለይቶ ለፍርድ የሚቀርቡበትን ስራ መስራቱ ላይ ነው። በህንድ ጥሪያችንን ሰምተው ትግላችንን የተቀላቀሉ ፍትህ ወዳድ እህትና ወንድሞች፣ ምስጋና ይገባቸዋል” በማለት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ ስለ ካሩቱሪ የተሰማውን ዜና አስመልክተው ተናግረዋል።
ሰንደቅ የተሰኘው ጋዜጣ ዜና ባለስልጣኖችንና የካሩቱሪን ሃላፊ አነጋግሮ ይፋ ያደረገው ዜና ኢህአዴግን የሚያሳፍር ከመሆኑም በላይ ከዝርፊያው በስተጀርባ ያሉትን በሙሉ ያስደነገጠ ሆኗል። የጎልጉል ምንጭ እንደሚሉት የጋምቤላ ድንግል መሬት በሳንቲም ሲቸበቸብ ከጀርባ ሆነው ኮሚሽን የተቀበሉና የሚቀበሉ ከፍተኛ ባለስልጣናትና ደላሎች አሉ። እነዚህ ሰዎች የአገሪቱን ሃብት በዓይነት፣ ገንዘቧን በብድር፣ ወገኖቻቸውን በጥይት እያስደበደቡ ለባዕድ በመስጠት የፈጸሙት ወንጀል መጨረሻ በራሳቸው አንደበት ይፋ ተደርጓል።
የአክሲዮን ሽያጩና የብድር ምንጩ የደረቀበት ካሩቱሪ ንብረቱ ለሃራጅ እንዲቀርብ በዝግጅት ላይ ነው። ሰንደቅ ባይገልጸውም ሼኽ መሐመድ ሁሴን አላሙዲ ሳዑዲ ስታር በሚባለው የግብርና ተቋማቸው ሰፊ መጠን ያለው መሬት በመውሰድ ህዝብ እንዲፈናቀል ካደረጉት ጋር እንደሚደመሩ በተለያየ ጊዜ የሚጠቆም ነው።