Tuesday, June 4, 2013

ተጠርጣሪዎች ከተከሳሽነት ወደ ምስክርነት

የፌደራል የስነምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን መረጃ ሳያሰባስብ ክስ መስርቶ ይረታል በሚል የሚታማ ተቋም ነው። ኮሚሽኑ ከጊዜ ወደጊዜ አቅሙንና ልምዱን በማዳበር ከዚህ ችግር መውጣቱን በዳታ አስደግፎ በመግለጽ ይከራከራል። አንድም ሰው ቢሆን ለምን ያለ በቂ ማስረጃ ይታሰራል ለሚለው የሰብአዊነትና የመብት ጥያቄ ያለመረጃ አስሮ ሲረታ ካሳ ስለመክፈሉና ላጠፋው ጥፋት የሚመጥን ቅታት ስለመቀጣቱ ተሰምቶ አያውቅም። የዘወትር ቅዳሜው ጋዜጣ አዲስ አድማስ በዚህ መልኩ ይሁን በሌላ አንድ አስገራሚ ዜና ይዞ ብቅ ብሏል።

ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣናት ጋር በተያያዘ የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ምርመራ ካካሄደባቸው 125 ተጠርጣሪዎች መካከል በ58 ላይ ክስ ሲመሰርት 52ቱ ከክስ ነፃ ሆነው በምስክርነት እንዲቀርቡ ሊደረግ መሆኑን ምንጮች ገልጾ አዲስ አድማስ አስታውቋል። በምስክርነት ለመቅረብ ተስማምተው ከክስ ነፃ ከሆኑት ምስክሮች መካከል አምስቱ ባለሃብቶች መሆናቸውና ሌሎቹ ደግሞ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን እንዲሁም በተጠርጣሪ ባለሃብቶች ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ መሆናቸውን አዲስ አድማስ አስታውቋል። ጋዜጣው ቀንጭቦ ያሰራጨው ዜና ሰዎቹ አስቀድሞ የታሰሩበትን ምክንያት አመልክቷል።

ከክስ ነፃ የሆኑት ምስክሮች ከሙስና ተጠርጣሪዎች ጋር ግንኙነት የነበራቸው ቢሆንም ተሳትፎአቸው በጅምር የቀረና ያልተፈፀመ መሆኑን የጠቆሙ ምንጮች፤ ለፀረሙስና ኮሚሽን ጥቆማ በመስጠት ለምርመራ ስራው አስተዋፅኦ ያደረጉ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ምስክሮቹን በቅርበት ስለሚያቋቸው ጉዳት ሊያደርሱባቸው ይችላሉ በሚል ማንነታቸው በሚስጥር እንደሚያዝ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ምስክርነት ከመስጠትም በተጨማሪ ገና ያልተያዙ ተጠርጣሪዎችንና ማስረጃዎችን በእነዚህ ምስክሮች አማካኝነት ለማግኘት እየተሞከረ ነው ተብሏል፡፡